Habakkuk 3

የዕንባቆም ጸሎት

1በዝማሬ የቀረበ የነቢዩ የዕንባቆም ጸሎት፤ በሺግዮኖት።
የሥነ ጽሑፍ ወይም የሙዚቃ ቋንቋ ሳይሆን አይቀርም።


2 እግዚአብሔር ሆይ፤ ዝናህን ሰምቻለሁ፤
እግዚአብሔር ሆይ፤ ሥራህም አስፈራኝ፤
በእኛ ዘመን አድሳቸው፤
በእኛም ጊዜ እንዲታወቁ አድርግ፤
በመዓት ጊዜ ምሕረትን ዐስብ።

3እግዚአብሔር ከቴማን፣
ቅዱሱም ከፋራን ተራራ መጣ። ሴላ
ትርጕሙ በትክክል የማይታወቅ ቢሆንም የዜማ ቃል ሳይሆን አይቀርም።

ክብሩ ሰማያትን ሸፈነ፤
ውዳሴውም ምድርን ሞላ።
4ጸዳሉ እንደ ፀሓይ ብርሃን ነው፤
ጨረር ከእጁ ወጣ፤
ኀይሉም በዚያ ተሰውሯል።
5መቅሠፍት በፊቱ ሄደ፤
ቸነፈርም እግር በእግር ተከተለው።
6ቆመ፤ ምድርን አንቀጠቀጠ፤
ተመለከተ፤ ሕዝቦችን አብረከረከ፤
የዘላለም ተራሮች ተፈረካከሱ፤
የጥንት ኰረብቶችም ፈራረሱ፤
መንገዱ ዘላለማዊ ነው።
7የኢትዮጵያ ድንኳኖች ሲጨነቁ፣
የምድያምም መኖሪያዎች ሲታወኩ አየሁ።

8 እግዚአብሔር ሆይ፤ በወንዞች ላይ ተቈጣህን?
መዓትህስ በምንጮች ላይ ነበርን?
በፈረሶችህና በድል አድራጊ ሠረገሎችህ
በጋለብህ ጊዜ፣
በባሕር ላይ ተቈጥተህ ነበርን?
9ቀስትህን አዘጋጀህ፤
ፍላጻም እንዲመጣልህ አዘዝህ፤ ሴላ
ምድርን በወንዞች ከፈልህ፤
10ተራሮች አዩህ፤ ተጨነቁም፤
የውሃ ሞገድ ዐልፎ ሄደ፤
ቀላዩ ደነፋ፤
ማዕበሉንም ወደ ላይ አነሣ።

11ከሚወረወሩ ፍላጾችህ፣
ከሚያብረቀርቅ የጦርህ ነጸብራቅ የተነሣም፣
ፀሓይና ጨረቃ በቦታቸው ቆሙ።
12በምድር ላይ በመዓት ተመላለስህ፤
ሕዝቦችንም በቍጣ ረገጥሃቸው።
13ሕዝብህን ለመታደግ፣
የቀባኸውንም ለማዳን ወጣህ፤
የክፋትን ምድር መሪ ቀጠቀጥህ፤
ከራስ ጠጕሩ እስከ እግር ጥፍሩም ዕርቃኑን አስቀረኸው። ሴላ
14እንደ ዐውሎ ነፋስ ሊበታትነን የመጣውን፣
ምስኪኑን በስውር በመዋጥ የሚደሰተውን፣
የሰራዊት አለቃ ራስ፣
በገዛ ጦሩ ወጋህ።
15ታላላቅ ውሆችን በመናጥ፣
ባሕሩን በፈረሶችህ ረገጥህ።
16እኔ ሰማሁ፤ ልቤም ደነገጠብኝ፤
ከንፈሬ ከድምፁ የተነሣ ተንቀጠቀጠ፤
ፍርሀት እስከ ዐጥንቴ ዘልቆ ገባ፤
እግሬም ተብረከረከ፤
ሆኖም በሚወርረን ሕዝብ ላይ እስኪመጣ ድረስ፣
የጥፋትን ቀን በትዕግሥት እጠባበቃለሁ።
17ምንም እንኳ የበለስ ዛፍ ባያፈራ፣
ከወይን ተክልም ፍሬ ባይገኝ፣
የወይራም ዛፍ ፍሬ ባይሰጥ፣
ዕርሻዎችም ሰብል ባይሰጡ፣
የበጎች ጕረኖ እንኳ ባዶውን ቢቀር፣
ላሞችም በበረት ውስጥ ባይገኙ፣
18እኔ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል፤
በድነቴ አምላክ ሐሤት አደርጋለሁ።

19ጌታ እግዚአብሔር ኀይሌ ነው፤
እግሮቼን እንደ ዋላ እግሮች ያደርጋል፤
በከፍታዎችም ላይ ያስሄደኛል።

ለመዘምራን አለቃ፣ በባለ አውታር መሣሪያዎቼ የተዘመረ መዝሙር።
Copyright information for AmhNASV